የሰሜን ወሎ ዞን በመስህብነት የተመዘገቡና ያልተመዘገቡ የተፈጥሮ; የታሪክና የባህል ቅርሶች የሚገኝበት ቦታ ነው፡፡ በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ቱሪስቶች የሚጎበኙ በርካታ የመስህብ ስፍራዎች ይገኛሉ፡፡
ዞኑ በአግባቡ ተጠንተው ከለላ ጥገናና እንክብካቤ ተደርጎላቸው ለቱሪስት አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉ በርካታ የተፈጥሮና ሰውሰራሽ መስኅቦች ባለቤትም ነው፡፡
ከነዚህም መካከል በወልዲያ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኘው የምስራቀ ፀሃይ ማመጫ ተ/ኃይማኖትና ክርስቶስ ሰምራ አንድነት ገዳም የሚጠቀስ ነው፡፡
ገዳሙ በተፈጥሮ ዋሻ የተመሰረተ ሲሆን ዋሻው ጥንታዊና ረዥም እድሜ ያስቆጠረ ነው፡፡ በዋሻው ውስጥ የአቡነ ተ/ኃይማኖትና ክርስቶስ ሰምራ ጽላቶች ይገኛሉ፡፡
ይህም ገዳሙ ሃማኖታዊ ክብረ በዓላት በሚከበርበት ጊዜና ለጸበል በሚመጡ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ምእመናን በሰፊው ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የገዳሙ መነኮሳት በተለያዬ ጊዜ በሚከሰት ድርቅ ምክንያት ለስደት እየተዳረጉ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም ወደ ገዳሙ የሚወስደው መንገድ ለትራንስፖርት አመቺ ባለመሆኑና በእግር ለመጓዝ በጣም አስቸጋሪ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ይህን ድንቅ ገዳም ለመጎብኘት አልቻለም፡፡
ገዳሙ ብዙ መሰረተ ልማት ያልተሟሉለት በመሆኑና በመንገዱ አስቸጋሪነት የአከባቢው ህብረተሰብ ከቱሪዝም ዘርፍ ያገኝ የነበረውን ጥቅም ማግኘት ሳይችል ቀርቷል፡፡
የማመጫ ተ/ሃ/ክ/ሰ/ አንድነት ገዳም ከዋሻው/ሽንቁሩ/ አከባቢ ጀምሮ ወደ ገዳሙ የሚወስደውን መንገድ ማሰራት ከተቻለ ወደ ገዳሙ ለአምልኮ ፣ ለጸበልና ለጉብኝት የሚመጡ ቱሪስቶችን ቁጥር መጨመርና እንዲሁም ከቱሪስት ፍሰት የሚገኝ ገቢን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግና የወልዲያና አካባቢው ህ/ሰብን እንዲሁም ገዳሙን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል፡፡
ስለሆነም ገዳሙ ለከተማችንና አካባቢው ህ/ሰብ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማስቻል የመንገዱ መሰራት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ስለሆነ መንገዱን ማሰራት እንዲቻል ለባለድርሻ አካላት ይህን ፕሮጀክት አቅርበናል፡፡