Build Your Dream

​ሰሜናዊት ሙሽራ

ወሩ ታህሳስ ወር ነው። የወልድያን የክብር ዶክተር ሼኽ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ ስታድየም ለማስመረቅ ኮሚቴዎች ተዋቅረው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። እንግዶችን የሚቀበሉ መቶ ቆነጃጅቶች ተመልምለዋል፤ የደህንነት ስራዎች ከስታድየሙና ከስታድየሙ ውጭ ተጧጡፏል። የስታድየሙን ምረቃ ህዝቡ በጉጉት የሚጠብቀው ሆኗል። ይሁንእንጅ የምረቃው ቀን አስር ጊዜ መቀያየሩ ህዝቡ በኮሚቴው ላይ እምነት እንዲያጣ አድርጎት ነበር።

በመጨረሻ ግን ጥር ስድስት የምረቃ ቀን ሆኖ ታወጀ፤ እንደሚታወቀው ጥር ወር የሰርግ ፣ የጥምቀትና በወልድያ በእጅጉ ልዩ በሆነ ሁኔታ የሚከበረው የጥር ሚካኤል ወር ነው። ብቻ ምን አለፋችሁ ወሩ በስታድየም ምረቃ ፣ በሰርግ ፣ በባዕላት ፣ በስዕልና ቅርፃቅርፅ ውድድር ፣ በባዛር የደመቀ የደስታ የፌሽታ ወር ሆኗል። 
ለዚህ ድግስ በከተማዋ በሚገኙ ሁሉም ቀበሌዎች ሴቶች ጤፉን እያበጠሩ፣ የጠላ ቂጣ እየጋገሩ የወልድያን የሰርግ ድግስ ለማሳመር ተያይዘውታል። ወንዱ ጌሾውን ይወቅጣል ፣ የጉልበት ስራዎችን ያግዛል። ያኔ ሴቱም ወንዱም ተባብሮ ሲሰራ ብታዩት እንዴት ደስ ይላል መሰላችሁ። ምን ነበር ሁሌም ትጉህ ብንሆንና ብንለወጥ ብሎ አርቆ ያስመኛል። አሁን ድግሱን ለማድመቅ የተለያዩ የአልኮል እና የለስላሳ መጠጦች ወደ ከተማዋ ገብተው ድግሱ በተዘጋጀባቸው በሁሉም የከተማዋ ቀበሌዎች በነፃ እየተከፋፈለ ነው። ሴቶቻችን ጤፋቸውን አበጥረው አስፈጭተው ሊጣቸውን አብክተው ጠላቸውን ጠምቀው ያን የደስታ ቀን “እስኪ ብቅ በይ ልይሽ” እያሉ በጉጉት ይጠባበቃሉ።
የወልድያ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት የድርሻውን ለመወጣት ሰራተኞቹ በስራ ተወጥረው ከኮሚቴዎቹ ጋር ጧት ማታ እየሰሩ ነው። እንግዳ ተቀባይ ቆነጃጅቶች መርጠው የአገር ባህል አልብሰዋል፤ የሐገሬውን ባህል ለማስተዋወቅና ለድግሱ ማድመቂያ ስነስርአት እንዲሆን ጅራፍ በአይነትና በእድሜ ለይተው አዘጋጅተዋል፤  የሙዚቃና ውዝዋዜ ስራዎች በወልድያና በጉባላፍቶ ባህል ቡድን ሊቀርብ ተሰናድቷል።
በጎን ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ለዘመናት ትቶት የኖረውን ከተማዋን የማልማት እና የማስዋብ ስራ በከፊል መንገዶች እንዲጠረጉ አድርጓል፤ በቆሻሻ የተሞሉ የጎርፍ መፋሰሻ ቦዮችን እንዲከፈቱና ከተማዋን በስፖርት ከለቡ ባንድራ ከዳር እስከዳር ቀለም እንዲቀባ ተደርጓል፤ የጋራ መፀዳጃ ቤቶች ሳይቀሩ ንፁህ እንዲሆኑና እድሳት እንዲደረግላቸውም፤ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫ ቶች በሁሉም የከተማዋ አቅጣጫ እንዲቀመጡ ተደርጎል፤ አደባባዮች ተሰርተዋል፤ አቧራ ለብሰው የኖሩ መንገዶች ኮብል ስቶን እንዲነጠፍላቸው ተደርጓል። ብቻ ምን ልበላችሁ ለድግሱ የሚደረገው ሽርጉድ ቁጭትንም ፣ ግርምትንም ፣ ትዝብትንም ይፈጥራል። ያኔ አስተዳደር አካላትን ያልታዘበ ሰው ይኖራል ብየ አላስብም። ይሁንእንጅ አሁንም ቢሆን ህዝባችን የሚፈልገው ልማትን በመሆኑ በዚሁ ቀጥሉበት ልመዱት እላለሁ።
ቀን ቀንን ሲተካ ወሩም ወርን ተክቶ አሁን ወሩ ጥር አንድ ብሏል። ከተማዋ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ሰው እጅጉን በዝቷል። ሰው ይበልጥ ምን ይፈጠር ይሆን ብሎ ደስታ ብቻ ሳይሆን ስጋትም ተጋብቶታል። ይሁንእንጅ በሁሉም ሰው ውስጥ የሰረፀው ለውጥና ቁጭት እንዲሁም ትዝብት ነው።
ከጥር 1 ጀምሮ ከተማዋ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ከዳር እስከዳር አሸብርቃለች መንገዱ ሁሉ የሰርግ ድንኳን የተጣለበት ይመስላል። አቤት ሲያምር! ምንነበር ሁልጊዜ እንዲህ በሆነና ህይወትን እንዲህ ጢባጥቤ ባልንባት ያለ ሰው አይጠፋም። ባነሮች በየቦታው እየተሰቀሉ ነው። ሰው ይሄ ሁሉ ሲሆን እውነትም ወልድያ መዳሯ ነው ማለት ጀምሯል።
ጥር 5 ሸኽ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲና ጠቅላይ ሚሙኒስቴር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ፣ ሚንስትሮችና የአማራ ክልል ባለስልጣናት ወልድያ ገብተው ያደሩበት የወልድያ ስታድየም ሰርግ ዋዜማ ነው። በዚያ ምሽት ሸኽ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲና ዶክተር አረጋ ከተማዋን በመኪና እየዞሩ በስማቸው የተሰየመውን አደባባይ እና የምስጋና ባነሮችን እየከፈቱ ነው። ህዝቡ ሊያያቸው ብቻ አይደለም ሊያቅፋቸው ሊስማቸው አብሯቸው ፎቶ ሊነሳ ወዲያ ወዲህ ይላል። ፌደራሎችም አንተ ከእሱ ተንቀሳቀስ! እያሉ ሰውን አሸብረውታል። ይሁንእንጅ መብትና ግዴታውን ያወቀ ህዝብ ነውና ቦታ አልሰጣቸውም። ሰው ገፍቶ ወደ ክብር እንግዶቹ ተጠጋ ሰላም ሊላቸው ባይችልም ፎቷቸውን በስልክ ካሜራቸው ያስቀሩ ሰዎች ግን ብዙ ናቸው። ቆነጃጅቶቻችነም በተፈጥሮ ወዛቸው አጊጠው ፣ ያሐገር ባህል ለብሰው ፣ ሹርባ ተሰርተው እንግዶቻችነን በደንብ ተቀበሏቸው። አቤት ደስ ሲሉ ከመልካቸው ማማር አንደበታቸው እንደ ትኩስ ማር መጣፈጡ ፣ የጨዋታ ለዛቸውስ፤ እኔ በወሎየነቴ የኮራሁበት ቀን ቢኖር ይህ ቀን ነው።
ጥር አምስት ከምሽቱ 3:00 ላይ አይን አይቶት ጆሮ ሰምቶት የማያውቀው ነገር መልካቆሌ ሜዳ ላይ ፈነዳ፤ ለወልድያ ብቻ ሳይሆን በዙሪያዋ ለሚገኙ ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች እንግዳ ነገር ነበር። ሁሉም በያለበት ከቤቱ ወጥቶ የርችት ትርኢቱን ይመለከታል። መጀመሪ ቀድሞ ላላወቀ ሰው መትረየስ የፈነዳ ወልድያ የጦር አውድማ የሆነች እንጅ የሰርጓ ማድመቂ አይመስለውም። በዚህም ምክኒያት ልጆቼን ጨረሷቸው ብለው ያለቀሱ ፣ ፀጉራቸውን የነጩ ፣ ደረታቸውን የመቱ ብዙ ናቸው።

Share:

More Posts

የቱሪዝም ምንነትና መስህብ ሀብቶቻችን

የአለም ህዝቦችን በማቀራረብ የባህል ልውውጥ እንዲኖር በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወት ትልቅ የኢንዱስትሪ መስክ እየሆነ መምጣቱ ሁሉም እየመሰከረለት የመጣ መስክ ነው፡፡ ሰዎች ለተለያዩ አላማዎች ከቦታ

የቅርስ ምንነት እና ትርጉም

ይዘት መግቢያ ሐገራችን ኢትዮጲያ ካላት የተፈጥሮ ሐብት ቀደምት ህዝቦች የስራ ውጤት የሆኑት ቅርሶች ባለቤት መሆኗ የሚታዎቅ ነው፡፡ ለምሳሌ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም የበርካታ ሰው ሰራሽና

ባህል የማንነታችን  መገለጫ ነዉ!

ባህል፡- እንደ ማህበረሰብ ሳይንስ አጥኝዎች ትርጉም የሰዉ ልጅ ባህርይ ፣ እምነት ፣ ዝንባሌ ፣ እሴት እና አስተሳሰብ እንዲሁም በማህበራዊ ኑሯቸዉ ዉስጥ የሚማሩት ፣ የሚፈጥሩት እና

 ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች

የሰው ልጅ በህይት ለመኖር መሰረታዊ ፍላጎቱ መርካት አለበት፡፡ ከዚህ ዉጭ የሚፈፅማቸው ግን ደባል ወይም ትርፍ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህም ትርፍ ነገሮች ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች ወይም

Send Us A Message

Scroll to Top