ወልድያ: ጥር 09/2017 ዓ.ም የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ የጥምቀት በዓል በወልድያ ከተማ ከ1770ዎቹ ጀምሮ በሃይማኖታዊ እና በባሕላዊ ክዋኔ እየተከበረ መቆየቱን ገልጸዋል።
ይህን የከተማዋን መገለጫ በዓል በማጉላት እስከ 2025 ዓ.ም ድረስ የጎብኝዎች መዳረሻ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
ለዚህም የሃይማኖት አባቶች ሃይማኖታዊ መልኩን፣ መንግሥት ደግሞ ማኅበረሰባዊ ኹነቱን አጉልቶ በመገንባት ሚናቸውን ለመወጣት መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያሉት።

የዚህ ዕቅድ ጅማሮ የኾነው የ2017 የጥምቀት በዓል በድምቀት እንዲከበር ከሃይማኖት አባቶች፣ ከወጣቶች ከጸጥታ አካላት እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር ብሎም ቀድመ ዝግጅት በማድረግ በዓሉን በሰላም ለማክበር ተሠርቷል ብለዋል።

ወልድያን እንደቀድሞ ስሟ ገነት ለማድረግ ከተያዙት ኘሮጀክቶች አንዱ የኾነውን የጥምቀት በዓል ድምቀት በማሳመር ማኅበረሰቡ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ነው ከንቲባው ያሳሰቡት።
ከአለባበስ እና ጭፈራ ጀምሮ ቀድሞ የነበረውን የከተማዋን ገጽታ የሚገነባ ክዋኔ እንዲኖር ወጣቱ ኀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
ከጸጥታ አኳያም የመንግሥት የጸጥታ መዋቅር የኅብረተሰቡን ደኅንነት ለመጠበቅ ዝግጅት ማጠናቀቁን ተናግረው ኅብረተሰቡም ራሱን እና ሃይማኖታዊ እሴቱን እንዲጠብቅ ጠይቀዋል።